ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስረኛ አመት ግንባታን በማስመልከት የበይነ መረብ ውይይት ተካሄደ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስረኛ አመት ግንባታን በማስመልከት የኢፌዴሪ ሚሲዮኖች፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የበይነ መረብ ውይይት ተካሄደ፡፡
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ባስተላለፉት መልዕክት ዳያስፖራውን በሚገባ ካስተባበርነውና ተሳትፎውን እንዲያሳድግ ከረዳነው ሃገርን የሚቀይር ዕምቅ አቅም እንዳለው የሃገራትን ተሞክሮ በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም ዳያስፖራው ሃብት ለማሰባሰብና የኢትዮጵያን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህን ለዓለም ለማስገንዘብ እያደረገ ላለው የፐብሊክ ዲፕማሲ ስራ ስጋናቸውን አቅርበው፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባባር ቦንድ መሸጥ ለማይቻልባቸው አካባቢዎች አማራጭ የሃብት ማሰባሰቢያ መንገድ መቀየሱን ጠቅሰዋል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ም/ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ በርሄም በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን ግድቡን በራሳቸው አቅም ጀምረው ለዚህ ደረጃ በማብቃታቸው ኩራት ሊሰማቸው እንደሚገባ ገልጸው፣ ቀሪ ስራዎችም ከፍተኛ ሃብትና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ የሚጠይቁ መሆናቸውን ታሳቢ በማድረግ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡በመድረኩ ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሑፍ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ም/ቤት ጽ/ቤት በኩል ቀርቧል፡፡በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ ክቡራን አምባሳደሮችና የሚሲዮን መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሃብት አሰባሰብ አንጻር የሚታዩ ደካማ ጎኖቹ በሚጠናከሩበትና አዳዲስ አሰራሮች በሚፈጠሩበት፣ ያሉ ጥንካሬዎችም ጎልብተው መሄድ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ሃሳብና አስተያየቶችን አንስተው ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡