(ግንቦት 05 ቀን 2014 ዓ.ም) በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የተመራው የልዑካን ቡድን በጀርመን ቆይታው ከጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች እና የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ጋር በሚሲዮኑ ጽ/ቤት የስብሰባ አዳራሽ ውይይት አድርገዋል።
በወቅቱ ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ከነባርና አዳዲስ የሚሲዮኑ ሰራተኞች ጋር ትውውቅ ያደረጉ ሲሆን በጀርመን የስራ ጉብኝት ስላደረጉበት አዲስ የሚሲዮን ጽ/ቤት ህንጻ ግንባታን በተመለከተ ከጀርመን መንግስት አካላት ጋር ስለነበረው ውጤታማ ውይይት ማብራርያ ሰጥተዋል።
ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ለሰራተኛው በሰጡት ምክረ-ሃሳብ አገራችን ባላት ውስን ኃብት ላይ ተመርኩዛ በምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ አሁን የሚታየውን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ቁመና ማየት የተቻለ መሆኑን በማንሳት የሚሲዮን ሰራተኞች ይህንን ከግምት በማስገባት የአገርን ክብር የመጠበቅና የአገር ጥቅምን የማስጠበቅ ድርብ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን አስገንዝበዋል። በጋራ መንፈስ (Team Spirit) መስራት ያስፈልጋል ያሉት ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ሙሉ ጊዜን ለዚሁ ትልቅ ኃላፊነት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
ክብርት ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን በማጠቃለያቸው የዜጎችን መብት ከማስጠበቅ፣ ዳያስፖራ ለአገር ጥቅም እንዲቆም ከማድረግና ዜጎች ከዩክሬን እንዲወጡ ከማድረግ አንጻር ሚሲዮኑ ለሰራው ስራ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን በተጨማሪም ዳያስፖራውና ምሁራን በተለያየ ዘርፍ ለአገራቸው በCOVID-19፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ መዋጮ፣ ለገበታ ለሀገር፣ ለአገር ሉዓላዊነት የማስከበር እና የተለያዩ ድጋፎች ላደረገው እንቅስቃሴ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ከዋናው መስርያ ቤት ለሚሲዮን ለሚያስፈልጉ የተለያዩ ጉዳዮች ድጋፎች በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸል።
በመጨረሻም ክብርት አምባሳደር ሙሉ ሰለሞንና የሚሲዮኑ ዲፕሎማቶችና ድጋፍ ሰራተኞች ስለተደረገላቸው ገለጻ ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይ ሙሉ አቅማቸውን አሟጠው በቅንጅት ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።