የዘንድሮው የአልበርት ኦስቫልድ የሄሰን የሰላም ሽልማት ዛሬ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተበረከተ
የዘንድሮው የጀርመኑ የአልበርት ኦስቫልድ ድርጅት የሄሰን የሰላም ሽልማት ዛሬ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተበርክቷል።
ዛሬ ከቀትር በፊት በሄሰን ፌደራዊ ግዛት ዋና ከተማ ቪስባደን በሚገኘው የፌደራል ግዛቱ ምክር ቤት በተከናወነው የሽልማት አስጣጥ ሥነ ሥርዓት የተገኙት የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል ሽልማቱን ተቀብለዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሄሰን ፌደራዊ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር የሄሰን ፓርላማ አባላት የጀርመን መንግሥት ባለሥልጣናት የተለያዩ ድርጅቶች ተወካዮች እና የኢትዮጵያ መንግሥት ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሰላም ሽልማቱ የተሰጣቸው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰላም ለማውረድ በመቻላቸው ነው።
የሄሰን የሰላም ሽልማት የቦርድ ስራ አመራር እና የሄሰን ፓርላማ ፕሬዝዳንት ቦሪስ ራየን፤ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለአፍሪቃ አህጉር ታላቅ ተስፋ ከተጣለባቸው መሪዎች አንዱ ናቸው” ሲሉ አመስግነዋቸዋል።
የሄሰን ፌደራዊ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር ፎከር ቡፋየርም ዐቢይ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ሰላም ካበረከቱት አስተዋጽኦ በተጨማሪ በአፍሪቃ ቀንድ ግጭቶችን ለማስወገድ የሚያደርጉትን ጥረትም ማድነቃቸውን ዶይቼ ቬለ ዘግቧል።