ከዳያስፖራ አባላት ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ምክክር ተካሄደ።
በበርሊን የሚገኘው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ ጥር 02 ቀን 2013 ዓ.ም ጀርመንን ጨምሮ ሚሲዮኑ ከሚሸፍናቸው ሌሎች ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ጋር #RisingEthiopia በሚል የሀገራችንን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ እ.ኤ.አ ዲሴምበር 30 ቀን 2020 ጀምሮ በተከፈተው የሁለት ወር ዘመቻ አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል።
ክብርት አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ብዙነህ በውይይቱ ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራችን የተለያዩ ጥንታዊ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሀይማኖት መገኛ ሀገር በመሆኗ፣ ያሏትን እሴቶች ለዓለም ለማስተዋወቅ ብዙ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በመሆኑም ሁሉም የዳያስፖራ አባላት ባላቸው የግንኙነት መረብ፣ ማህበራዊ ሚዲያ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ዘመቻውን በመቀላቀል፣ የሚወጡ መረጃዎችን በማጋራት አገራችውን በበጎ መልኩ በማስተዋወቅ ያለባቸውን አገራዊ ሃላፊነት እንዲወጡ ከአደራ ጭምር አሳስበዋል።
ተሳታፊዎችም በበኩላቸው ዘመቻው ከተጀመረ ጀምሮ እየተሳተፉ መሆኑን በመግለጽ፣ አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ያልተነገረለት የባህል፣ የተፈጥሮ ሃብት፣ የታሪክ እና የቅርስ ሃብት ያላት በመሆኑ፣ ይህንን ለዓለም በማስተዋወቅ ለአገራችን ልማት እና ብልጽግና ማዋል እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
The Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia
Spokesperson Office of the Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia