በጀርመን ፌዴራል ሪፐብሊክ፣ በቼክ ሪፐብሊክ፣ በፖላንድ ሪፐብሊክ፤ በስሎቫክ ሪፐብሊክ እና በዩክሬን ሪፐብሊክ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን፤ ትውልደ-ኢትዮጵያውንና የኢትዮጵያ ወዳጆች አደረጃጀቶች ጋር ሀገራዊ የድጋፍ ጥሪን በተመለከተ ውይይት ተደረገ
በጀርመን ፌዴራል ሪፐብሊክ፣ በቼክ ሪፐብሊክ፣ በፖላንድ ሪፐብሊክ፤ በስሎቫክ ሪፐብሊክ እና ዩክሬን ሪፐብሊክ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፤ ትውልደ-ኢትዮጵያው እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ማህበራት ሀላፊዎችና አባላት እንዲሁም የዳያስፖራ ፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲ አደረጃጀቶች ጋር ሀገራዊ የድጋፍ ጥሪን በተመለከተ መስከረም 11 ቀን 2015 የበይነ-መረብ ውይይት ተካሂዷል።
በበርሊን የኢትዮጵያ ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮነ መሪ የሆኑት አምባሳደር ተፈሪ ታደሰ ባደረጉት ንግግር አሸባሪው የህወሐት ቡድን ሶስተኛ ዙር ጥቃት በመክፈቱ በዜጎቻችን ላይ እያደረሰ ያለውን ሞት እና እንግልት እንዲሁም የንብረት ውድመት በማስቀረትና መልሶ በማልማት ረገድ የሁሉም አገር ወዳድ ተሳትፎና ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚያስፈልግበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምንገኝ ጠቅሰው፤ ከዚህ በፊት በነበረው ጥቃት በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ ትውልደ-ኢትዮጵያውንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ተሳትፎና ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰው፤ ሀገራዊ የድጋፍ ጥሪውን በተመለከተ የሚሲዮኑ ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች እስከ 4 ወር የሚደርስ ደመወዛቸውን መስጠታቸውን እንዲሁም 12,300.00 ዩሮ ያህል ለህዳሴ ግደቡ ማዋጣታቸውን፤ በኑረንበርን ከተማ ነዋሪ የሆኑት ኢትዮ-ብሪጅ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ለአገራዊ ጥሪው 9,000.00 ዩሮ ድጋፍ ማድረጋቸውን እና በዱዙንዶልፍና አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያነ ለህዳቤ ግደቡ 4,100.00 ዩሮ በስጦታ መለገሳቸውን በመግለጽ ሌሎቻችንም ለሀገራዊ ጥሪው የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናድርግ በሚል ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የዳያስፖራ አባላት በውይይቱ ወቅት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ ትውልደ-ኢትዮጵያውና የኢትዮጵያ ወዳጆች በፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲው አውድ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እውነታዎች በትክክል እንዲገነዘብ ያደርጉት የነበረውን ተሳትፎ የበለጠ በተቀናጀ አግባብ አጠናክረው ለመቀጠል፣ እንዲሁም ለቀረበው ሀገራዊ ጥሪ የበኩላቸውን ድጋፍ ለማበርከት አበክረው እንደሚሰሩ ያረጋገጡ ሲሆን፣ ለዚህም እንዲያግዝ ሁሉም አደረጃጀቶች ለሀገራዊ ጥሪው በከፍተኛ ተሳትፎ እንደሚንቀሳቀሱና በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
በመጨረሻም በጀርመን፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፖላንድ፤ ስሎቫክ እና ዩክሬን የኢትዮጵያ ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ተባብረን እንረባረብ፤ ካለው ጊዜ አኳያ እያንዳንዱ ግለሰብ፤ ማህበራት፤ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እና የሀይማኖት ተቋማት ለሀገራዊ ጥሪው የሚጠበቅባቸውን በመወጣትና በማስተባበር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ስለዳያስፖራው ተነሳሽነት፤ ቁጥርኝነትና የሀገር ፍቅር ወኔ አመስግነዋል፡፡