የአንድነት በዓል በኢትዮጵያ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ በርሊን ጳጉሜ 5 ቀን 2014 ዓ.ም በዙም ተከበረ።
የኢትዮጵያ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ በርሊን ጳጉሜ 5 ቀን 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተገኙበት የአንድነት በዓልን በዙም አክብሯል። በፕሮግራሙ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ በክብር የተጋበዙት ሁለት ተናጋሪዎች.፣ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የኢትዮጵያን ተሞክር በአንድነት ዙሪያ ያቀረቡ ሲሆን፣ ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ የአውሮፓን ተሞክሮ አቅርበዋል።
ፐሮግራሙ በክብርት አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን በጀርመን ፌደራላዊ ሪፓብሊክ፣ ፖላንድ ሪፓብሊክ፣ ቼክ ሪፓብሊክ፣ ስሎቫክ ሪፓብሊክ እና ዩክሬን የኢትዮጵያ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር እንኳን ደህና መጣች መልዕክት የተጀመረ ሲሆን አምባሳደር ሙሉ ተሳታፊዎችን እንዲሁም አቅራቢዎች ጥሪውን በማክበር በመገኘታቸው አመስግነዋል።
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴም የአንድነት መገለጫዎችን በሶስት ረድፍ ከፋፍለው አቅርበዋ፣ እነዚህም አንደኛ የአንድነት መገለጫ ሁለተኛ የአንድነት ፈተናዎች ሶስተኛ የወደፊት አቅጣጫዎች እና እጣፈንታ ሲሆኑ፣ መገለጫዎችን በተመለከተ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ሰማንያ ቋንቋዎች የሚነገሩባት አገር ብትሆንም ቋንቋዎቹ በአራት የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ እንደሚካተቱ ገልጸው የቋንቋዎቹ የመወራረስ ባህሪዎችን አስረድተዋል።ፕሮፌሰር ጨምረው ሌላው መገለጫ ዘላቂ የሆነ የታሪክ ትስስር እንደነበረ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስታት. በታሪክ ውስጥ ህብረ ብሄራዊ ባህርይ እነዳላቸው አትተዋል። በተጨማሪ አንድነትን የሚያሳዩት ባህርያት ከብሄር ማንነት በላይ መሆናቸውን ማጤን እንደሚገባ ገልጸው በዚህ መልኩ አንድነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል አስምረዋል።
ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ በበኩላቸው አንድነትን ከብዝሀነት እና ከአውሮፓ ተሞክሮ አንጻር አስረድተዋል። ዶ/ር ፀጋዬ እንደገለጹት አንድን ተግባር ማቃናት እና ማሳካት የሚቻለው በአንድ ላይ ሲሳለጥ መሆኑን አስገንዝበዋል። የጀርመን ተሞክሮን በማንሳትም ምንም እንኳን ጀርመኖች በታሪካቸው ግላዊነት የታይባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም የጀርመን ማንነትን ለመገንባት በእንድ ላይ መስራታቸውን ገልጸዋል።እንደተጠቃሽም በማንሳት በማርች አብዮት ወቅት ከክልል ማንነት ወደ አገራዊ ማንነት ለማምጣት መሰራቱን አስረድተዋል።
በማጠቃለያ አምባሳደር ሙሉ በአሁኑ ወቅት በምን መልኩ አንድነትን እና ሉአላዊነታችንን መጠበቅ እንዳለብን የገለጹ ሲሆን ኢትዮጵያ የሁሉም አገር ብለን ማመን በፍቅር መኖርን እንደሚያስችል እንዲሁም በአንድነት እናሸንፋለን ከችግሮች ሁሉ በላይ ነን ብለን ማመን ይኖርብናል ብለዋል። አገራችን ለኛ ምን አድርጋልናለች ብለን ከመጠየቃችንም በፊት እኛ ለአገራቸን ምን እናድርግ ማለት እንዳለብን አሳስበዋል።
በመጫረሻም ከተሳታፊዎች ውይይት በኃላ ተሣታፊዎች፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅ በዘር፣በቋንቋ፣በሃይማኖት፣ በቀለም እና በአስተሳሰብ ልዩነቶች ሳይገደቡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ክብርና ዝናዋን ከፍ ለማድረግ የሚጠበቀውን የዜግነት ግዴታ ለመወጣት ቃለ መሃላ በመፈጸም በኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙር ፕሮግራሙ ተዘግቷል።