የኢትዮ-ቼክ ኮሚኒቲ ማህበር በይፋ ሥራ መጀመሩ ተገለፀ
ክብርት አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን በጀርመን ፌደራላዊ ሪፓብሊክ፣ ቼክ ሪፓብሊክ ፣ፖላንድ ሪፓብሊክ ፣ስሎቫክ ሪፓብሊክ እና ዩክሬን የኢትዮጵያ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር በክብር እንግድነት በቼክ ዋና ከተማ በፕራግ በመገኘት የኢትዮ- ቼክ ማህበር መቋቋሙን በይፋ አበሠሩ ክብርት አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ማህበሩ የተቋቋመው ኢትዮጵያን ለመርዳት በሚደረገው ጥረት የራሳቸውን ከፍተኛ ሚና ለመወጣት እና እርስ በእርስ ለመረዳዳት ፈቃደኛ በሆኑ የዲያስፖራ አባላት በመሆኑ አድንቀዋል፡፡ ማህበሩ ጠንካራ ራዕይ ይዞ የተነሣ በመሆኑ ከምንግዜውም በላይ በልዩ ልዩ ሙያ የተሠማሩ የዲያስፖራ አባላትን ይዟል ፡፡ ለምሳሌ፡ የህክምና ዶክተሮች፣ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች እና ተማሪዎችን ጭምር አካቷል።
አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ባደረጉት ንግግር የማህበር አባል መሆን ለመጠቀም ብቻ ሣይሆን ለመጥቀምና ለመሰጠት መሆን እንዳለበት ገልፀው ጊዜን፣ ገንዘብን፣ እውቀትን ለማህበረሰብ ግልጋሎት መስጠት ፣ በገንዘብ የማይተመን እርካታ ስለሚሰጥ በሙያ ፣በገንዘብ ፣ በልዩ ልዩ አቅም አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ፣ ማህበሩን ያልተቀላቀሉ ካሉ አንዲቀላቀሉ እና አባል የሆኑ ያለጥቅም ሀገርንና ወገንን ለመርዳት በቁርጠኝነት በመስራት ምሣሌ እንዲሆኑ አሳስበዋል ።
በእለቱ ከተስበስቡት አባላት፣ የቆንስላ አገልግሎት ማግኘት የሚፈልጉ እና ለህዳሴ ግድብ ቦንድ ለመግዛት የሚፈልጉ ተመዝግበዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ ዓመት የተስፋ ስሜትን እና ደስታን የሚቀሰቅሱ ሙዚቃዎች ቀርበዋል ።
የማህበሩ መስራች እና ፕሬዝደንት አቶ ተሻለ ሽበሽ በበአሉ ላይ ባደረጉት ንግግር በቼክ ሪፐብሊክ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተጠናከረ ህጋዊ የሆነ ኢትዮ-ቼክ ኮሚኒቲ ማህበር በማቋቋም ጷጉሜ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ማህበሩ በይፋ ስራ መጀመሩን እና የአድነትን ቀን በአልን ደርበው ክብርት አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ብዙነህ በተገኙበት ማክበሩን በደስታ ገልፀዋል፡፡
ቀጥለው መንግስት የያዘው የዜጋ ተኮር ፖሊሲ አድንቀው ፣ ቀድሞ ከተለመደው ውጭ ክብርት አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ወደ ኮሚኒቲው ወርደው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እርስበር መተባበራቸውን እንዲያጠናክሩ እያደርጉ ያለውን የማበረታታት ተግባር አድንቀዋል።
በመቀጠል ኢትዮ-ቼክ ኮሚኒቲ ማህበር የተመሰረተበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ በቼክ ሪፕብሊክ እና በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮ- ቼካዊያን ማህበር ሣይኖራቸው ለበርካታ አመታት በግለሰቦች ፈቃድ ለዓመት በዓላት ሲገነኙ መቆየታቸውን ጠቅሰው፣ ነገር ግን በመደራጀት የተሻለ ሥራ መስራት ስለሚቻል በጋራ አቅምን እጎክብቶ ተሠሚነት ለማግኘትና የኮሚኒቲውን መብት ለማስከበር፣ እንዲሁም የማህበረሰባችንን ችግሮች በጋራ ለመፍታትና ለመቋቋም ፣ ድንቅ የሆኑ የጋራ ባህላዊ እሴቶቻችንን ለመጠበቅ እና ለማስተዋወቅ ፣ ከምንኖርበት ሀገር ባህል ህግና የኑሮ ዘይቤ ጋር በማጣጣም ውጤታማ እንድንሆን በሁለንተናዊ መልኩ የሚያግዝ፣ ከማንኛውም የዘር፣የፖለቲካና የሐይማኖት አመለካከት ልዩነቶች ነፃ የሆነ ጠንካራ ማህበር እንዲኖረን እራሳችንንና ሀገራችንን ለመርዳት ባለንበት ሀገር የተከበርን ዜጋ ለመሆን በመፈለግና እንዲሁም የእርስ በርስ የመቀራረብ፣ የመግባባት፣ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህላችንን በማዳበር የተለያዩ ድጋፎችንም ለወገን መስጠት እንድንችል በማሰብ ሁሉን አቀፍ የሆነ ኢትዮ-ቼክ ኮሚኒቲ ማህበር በሚል ስያሜ በእ.ኤ.አ. 15.07.2022 ማህበር በማቋቋም ዛሬ ማህበሩ ስራ መጀመሩን በይፋ በመገለፁ፣ ደሥታቸውን ገልፀዋል።
በመጨረሻም ‘”ሁሉም የሚናፍቋት እናት ሃገራችን ያለችበት ሁኔታ የአደባባይ ሚስጥር በመሆኑ፣ ከምንግዜውም በተለየ ሁኔታ ዛሬ የልጆቿን ድጋፍ እና እርዳታ የምትፈልግበትም ወቅት በመሆኑ እኛ በቼክ ሪፕብሊክ ያለን ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በሚገባ እንረዳለን፣ በሚያስፈልገው ሁሉ እና በዲጅታል ዘመቻው የIinternational community እያሳደረባት ያለውን ጫናንም በመከላከል ከጎኗ መሆናችንን ልናሳውቅ እንወዳለ” ብለዋል።