(ኢ ፕ ድ)
የኢትዮ-ጀርመን ፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴሰብሳቢ ዶ/ር ዲማ ነገዎ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ጀርመን ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የጀርመን የፓርላማ ልዑክ ቡድን ጋር ተወያይተዋል።
ሀገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ ብትሆንም በሀገሪቱ ተፈጥሮ በነበረው ጦርነትና በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው የድርቅ አደጋ ሳቢያ ሀገሪቱን በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጠሟት ቢሆንም እነዚህን ፈተናዎች ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች ብለዋል ሰብሳቢው።
በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰበት የትግራይ ህዝብ መንግስት በየብስና በአየር ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረስ ላይ እንደሚገኝም ለሉዑካን ቡድኑ አባላት ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥም ሀገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽንን በማቋቋም የሚታዩ የልዩነት ሀሳቦችን ሁሉም አካላት በማሳተፍ በውይይትና በምክክር ለመፍታት እንዲቻል መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡
አክለውም ኢትዮጵያ ከድህነት ለመላቀቅ “ግድቡ የኔ ነው” በሚል መፈክር በራሷ ህዝቦች መዋጮ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ እንደምትገኝ፣ ግድቡም የሌሎችን ሀገሮች ጥቅም የማይጎዳ እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም ጀርመን ከሀገሪቱ ጋር ባላት ጠንካራ ግንኙነት በቴክኖሎጂ እየደገፈች እንደምትገኝ ጠቁመው ወደፊትም በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በቴክኒክ እንዲሁም ተቋማትን መልሶ በመገንባት ረገድ ድጋፏን እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡
የጀርመን ፓርላማ አባል የሆኑት የተከበሩ ሮድሪች ኪይስዌተር በበኩላቸው ሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ወዳኝነት ያላቸው መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ጀርመን ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ በተለይ በቴሌኮም ዘርፍ እየደገፈች መሆኑን አስታውሰው በቀጣይም በትምህርት፣ በልምድ ልውውጥ እና በቴክኒክ ረገድ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።