የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አሁርን በዛሬው ዕለት በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
ሐምሌ 18 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ: የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር የሆኑትን ስቴፋን አሁርን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው በነጋገሩበት ወቅት፤ ኢትዮጵያና ጀርመን ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ ሀገራት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ቀደም ሲልም የጀርመን መንግስት ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግስት እየሰራቸው ላሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ስኬታማነት የበኩሉን እገዛ ሲያደርግ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሀገሪቱ የተካሄደውን አዲስ የመንግስት ምስረታን ተከትሎ እንደአዲስ መዋቀሩንና በርካታ ሃላፊነቶች እንደተጣለበትም በሰፊው አብራርተዋል፡፡ ሃላፊነቱን ከመወጣት አኳያም በየዘርፉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን፣ ፕሮግራሞችንና እቅዶችን ነድፎ ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በተለይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላምን በማስፈንና ልማትን በማፋጠን ረገድ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ያላቸውን ድርሻና ሚና ለማጎልበት ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛልም ብለዋል፡፡
በየዘርፉ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ቢሆንም ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ከማስቻል አኳያ በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም እንደአገር ለሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት የጀርመን መንግስት ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሚኒስትሯ ክብርት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ጠይቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አሁር በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሴቶችን በማብቃት፣ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሰፊው እንዲሰማሩ በማስቻል፣ ሴቶችና ወጣቶች ጨምሮ አደረጃጀቶች ለሀገር ሰላምና ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ እየተሰራ መሆኑ፣ በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች ከሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር የሳይኮ ሶሻል ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑ እንዲሁም መንግስት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት ከልብ አድንቀዋል፡፡ እንደአገር እየተካሄደ ያለውን የሪፎርም ስራም እንደሚደግፉት አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይም በሰላም ግንባታ፣ ሴቶችን በማብቃት፣ ሰብዓዊ ድጋፎችን ተደራሽ በማድረግ፣ በታዳሽ ሀይል አቅርቦት በሌሎችም መስኮች ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው ተግባራት ውጤታማነት ጀርመን የበኩሏን ድጋፍ እንደምታደርግ እንዲሁም በሁለቱ ወዳጅ ሀገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትኩረት እንደሚሰሩ አምባሳደር ስቴፋን አሁር ቃል ገብተዋል፡፡
ምንጭ፡-የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፌስ ቡክ ገፅ