የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት አራተኛ ዓመት ክብረ በዓል በፍራንክፈርትና አካባቢው
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት አራተኛ አመት በፍራንክፈርትና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች በተገኙበት” እንዳጋመስነው እንጨርሰዋለን ሌላም እንጀምራለን” በሚል መሪ ቃል በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል። በእለቱ የተገኙ የፕሮግራሙ የክብር እንግዳ የኢትዮጵያ የሰላምና ልማት ኢንስቲቱት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስብሀት ነጋ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለዘመናት ነግሶ የነበረውን ኢፍትሃዊ የአባይ ውሃ አጠቃቀም የሰበረ፣ የጋራ ተጠቃሚነትና የይቻላል አስተሳሰብን ያሰፈነ እንዲሁም አግባብነት የጎደለው አስተሳሰብና አቋም በማራመድ ላይ የነበሩ አካላት ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲይዙ ያደረገ ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀዋል።
በጀርመን አገር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ ክቡር አምባሳደር ኩማ ደመቅሳ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የህዳሴ ግድብ መሰረት የተጣለበት 4ኛ አመት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎችና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እየተከበረ መሆኑን ገልፀው፣ ይህ በዓል በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ያለው ከዚህ በፊት ግድቡ ሲጀመር ህዝቡ አንግቦት በነበረው መሪ ሀሳብ ማለትም “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን” በሚል ሳይሆን “እንዳጋመስነው እንጨርሰዋለን ሌላም እንጀምራለን” እንደሆነ ጠቅሰው፣ የአገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ የተለያዩ ተጨማሪ ግድቦች፣ ፋብሪካዎች፣ የባቡር መስመሮችና መንገዶች ያስፈልጉናል ብለዋል።
በተጨማሪም ክቡር አምባሳደሩ የግድቡ ግንባታ ሀገራዊ መግባባትን የፈጠረ በመሆኑ በ2007 አገራዊ ምርጫ እየተሳተፉ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሳይቀሩ ለግድቡ ግንባታ ያላቸውን ከፍተኛ ድጋፍ እየገለፁ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ ሁሉም አካላት ግድቡ የእገሌና የእገሊት የዚህኛው ፓርቲ ወይም የዛኛው ፓርቲ ተብሎ ልዩነት መደረግ የሌለበት እንደሆነ በማስገንዘብ ርብርብ መደረግ አለበት የሚል አቋም እያንፀባረቁ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በፍራንክፈርት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ቆንስል ጄኔራል አቶ ምህረተአብ ሙሉጌታ ደግሞ ለተሳታፊዎች እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ፋይዳው የጎላና ታላቅ ፕሮጀክት በመሆኑ የተጀመረው ርብርብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፋል።በመጨረሻም በምእራብ ጀርመን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምክር ቤት ከተቋቋመ ጀምሮ እስከአሁን ከ16 ሚሊዮን ብር በአከባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች መሰብሰብ እንደቻለ የምክር ቤቱ ዋና ሰብሳቢ አቶ መላኩ አልማው ገልፀዋል። በተጨማሪም የህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት አራተኛ ዓመት ክብረ በዓል ዝግጅት ላይ የ277,500.00 ብር የቦንድ ሽያጭ ለማከናወን ተችሏል፡፡ በመሆኑም ዘገባው በናንተ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንዲተላለፍ የተለመደውን የስራ ትብብራችሁ እየጠየቅን ለዜና የሚሆን ከታች የተገለፀውን ሊንክ እንድትጠቀሙ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡
1. http://youtu.be/atJTZo0CeeA
2. http://youtu.be/Zjzfi950uds
“እንዳጋመስነው እንጨርሰዋለን ሌላም እንጀምራለን” !!!