
News


ከኢትዮጵያውያን፤ ትውልደ-ኢትዮጵያውንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር ሀገራዊ የድጋፍ ጥሪን በተመለከተ ሳምንታዊ ውይይት ተደረገ
በጀርመን ፌዴራል ሪፐብሊክ፣ በቼክ ሪፐብሊክ፣ በፖላንድ ሪፐብሊክ፤ በስሎቫክ ሪፐብሊክ እና ዩክሬን ሪፐብሊክ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፤ ትውልደ-ኢትዮጵያው እና የኢትዮጵያ ወዳጆች፤ ማህበራት ሀላፊዎችና አባላት እንዲሁም የዳያስፖራ ፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲ አደረጃጀቶች ጋር ሀገራዊ የድጋፍ ጥሪን በተመለከተ መስከረም 23 ቀን 2015 የበይነ-መረብ ውይይት ተካሂዷል።
በጀርመን ሪፐብሊክ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፖላንድ ሪፐብሊክ፤ ስሎቫክ ሪፐብሊክ እና ዩክሬን የኢትዮጵያ ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና ልዩ መልእክተኛ ክብርት አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ ሁሌም በሀገር ጉዳይ ሲጠሩ ቅድሚያ በመስጠት ሀገራችን የቁርጥ ቀን ልጆች እንዳሏት በየጊዜው እያስመሰከሩ መሆኑን በመግለጽ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ ሌሎችን በማስተባበር ይህንን የሀገር ወሳኝ የድጋፍ ጥሪ ምላሽ በመስጠት ረገድ የበለጠ እንዲሰሩ አደራ በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ እስከአሁን እያደረጉ ስላሉት ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
በሚሲዮኑ የዲያስፖራ ዘርፍ እስከ አሁን ለሀገራዊ የድጋፍ ጥሪ ስለተደረጉ ድጋፎችንና ቃል ስለተገቡት ገለፃ የተደረገ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪ ለድጋፍ ማሰባሰቢያ ስለተዘጋጀው የቃል መግቢያ ሶፍትዌር ዝርዝር ገለፃ ተደርጓል፡፡
የዳያስፖራው አባላት ለቀረበው ሀገራዊ ጥሪ የበኩላቸውን ድጋፍ በማበርከት ረገድ በየተደራጁበት ማህራት ድጋፍ የማሰባሰቡ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንና ለዚህም የቶምቦላ ሽያጭ ጭምር እየተከናወነ እንደሆነ በመግለጽ ሁሉም አደረጃጀቶች ለሀገራዊ ጥሪው በከፍተኛ ተሳትፎና ቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑና እስከአሁን ያሰባሰቡትን የገንዘብ መጠን ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለያየ የሙያ መስክ ላይ የተሰማሩት የዳያስፖራ አባላት ያላቸውን እውቀት ወደ አገራቸው ማስተላለፍ እንደሚፈልጉ በመግለጽ ከሚሲዮኑ ጋር ተቀራርበው ለመስራት ተስማምተዋል ።
በበርሊን የኢትዮጵያ ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮነ መሪ የሆኑት አምባሳደር ተፈሪ ታደሰ ባደረጉት ንግግር ሚሲዮኑ በቀጣይ በተደራጀ መልኩ ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር በጋራ እንደሚሰራ በመግለጽ ሁላችንም ተረባርበን ለዚህ የሀገራዊ ጥሪ ተሳትፎችንን አጠናክረን እንቀጥል በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም ክብርት አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ተባብረን እንረባረብ እንረባረብ፤ በአሁኑ ጊዜ ህዝቡን የመከፋፈል ሴራ ሀገርን እየፈተነ ያለው ከውስጥና ከውጪ መሆኑን በመረዳት ውስጣችንን በመፈተሽ መከፋፈልን አስወግደን በጋራ በጥንካሬ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆናችንን በትብብርና በአንድነት በመቆም ሀገራዊ የድጋፍ ጥሪው እንዲቀጥል በማስተባበር የበኩላችንን እንወጣ በሚል ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ስለዳያስፖራው ተነሳሽነት፤ ቁጥርኝነትና የሀገር ፍቅር ወኔም አመስግነዋል፡፡

መንግስት ያቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከ1.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሰባሰበ
መንግስት ያቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኢፌዴሪ ሚሲዮኖች አስተባባሪነት በተከናወነ የሀብት ማሰባሰብ ሂደት በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከ1.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሰባሰበ።
ከተሰባሰበው ገንዘብ ውስጥ 1.4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር፣ 59.3 ሺህ ዩሮ እንዲሁም 53 ሺህ ፓውንድ የሚገኝበት ሲሆን፣ 35 ሺህ የአሜሪካን ዶላርና 8ሺህ ዩሮም ቃል ተገብቷል።
በዚሁ ጊዜ ውስጥ ከ8 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች መሰባሰባቸውም ታውቋል።
በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለተሰባሰበው ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት ምስጋናው እያቀረበ፣ ዳያስፖራው በሚሲዮኖች አስተባባሪነት በኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስቴር በተዘጋጁት አካውንት ቁጥሮች ማለትም ለዩሮ (1000439142832)፣ ለዶላር (1000439142786) እንዲሁም ለፓውንድ (1000443606304) በመጠቀም ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ የአይዞን ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ አማራጭን (https://eyezonethiopia.com) በመጠቀም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን ያቀርባል።
