በበርሊን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ በጀርመንና ሚሲዮኑ በሚሸፍናቸው አገራት ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልድ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተገኙበት የ2018 ዓ.ም. የኅብር ቀን በአንድነት አክብሯል፡፡

የ2018 ዓመት የጳጉሜን ወርና ቀናት “የአትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበሩ መሆኑን ተከትሎ ሚሲዮኑ ጳጉሜን 4 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚከረውን የህብር ቀን ’’ብዝሃነታችን ጌጣችን’’ በሚል መሪ ቃል አከብሯል።

በበዓሉ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የሚሲዮኑ መሪ አምባሳደር እስክንድር ይርጋ እለቱ መጪው የ2019 አዲስ አመት የኢትዮጵያን ማንሰራራት በሚገባው ከፍታ ለማድረስ በህብረብሔራዊነት ውስጥ ያለውን አንድነት እና ጥንካሬ በመጠቀም ቀጣይ ድሎችን የማስመዝገብ ጉዞ የሚረጋገጥበት እንደሚሆን አብስረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ፣ ጠንካራ እና የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ሀገር መሆኗን ገልፀው፣ ከሚያለያዩን ይልቅ በሚያስታሳስሩን የጋራ ትርክቶች እና ሃብቶች ላይ በመመርኮዝ፣ ባለፈው አመት የተመዘገቡ አስገራሚ ስኬቶችን በማስቀጠል ብሎም ተግዳሮቶችን በመፍታት የኢትዮጵያን ማንሰራራት እውን እናድርግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በበዓል ዝግጅቱ የህጻናት የአዲስ አመት ዝማሬ፣ ያለፈውን አመት አገራዊ ድሎች የሚያሳይ ዘጋቢ አጭር ፊልም እና በዳያስፖራ አደረጃጀት ተወካዮች የአብሮነት መልእክቶች ተላልፈዋል፡፡ ታዳሚዎች በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል።